የጥሞና ቃል ክፍል 24

“የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችን ባየሁ ጊዜ፥ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን

ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?”(መዝ. 8፥3-4)

የሰው ልጆች ሁሉ ፌደራል አባት አዳም ባለመታዘዝ ኃጢአት ከወደቀበት ጊዜ አንስቶ ከእግዚአብሔር የመሸሽ ዝንባሌ የሰው ሁሉ ባሕርያዊ ጠባይ ሆኗል። አዳምና ሔዋን “ከእግዚአብሔር ከአምላክ ፊት በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ” ይላል (ዘፍ. 3፥8)። እግዚአብሔር አምላክም “ጠርቶ፦ ወዴት ነህ? አለው”። እግዚአብሔር አዳም የት እንዳለ ጠፍቶት ሳይሆን አዳም ይህንን የአምላኩን የፍቅር ጥሪ ሰምቶ የት እንደወደቀና እንዳለ እንዲገነዘብ ያለመ ጥሪ ይመስላል። ዛሬም ይህ አማላክዊ የምሕረት ጥሪ በሰው ልጆች ሁሉ ይሰተጋባል። የት ነኝ ያለሁት? ከእግዚአብሔር ጋር ያለኝ ቅርበትና ርቀት ምን ይመስላል? ብለን ከእንቅልፉ እንደሚባንን ሰው ብድግ ብለን ወደ አምላካችን እቅፍ ጉያ መግባት ይኖርብናል። ከዚህ ድምጽ ስንርቅ መንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ እንገባለን። የምንመላለስበትና የምንሄድበት አካሄድ ሁሉ ጨለማን የተላበሰ ይሆናል ማለት ነው። እግዚአብሔር ግን ብርሃን ነው። በጨለማ ሕይወት ጣልቃ እየገባ የክርስቶስ ወንጌል ብርሃን ያበራልናል። ይህም እኛን ወደ ፍቅሩ መንግሥት እቅፍ ይመልሰን ዘንድ ያደረገው መለኮታዊ አሠራር እግዚአብሔር በምሕረቱ ብዛት እንዳሰበን ያሳያል። ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ወክሎ ኃጢአታችንን ተሸክሞ ይሞት ዘንድ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የታቀደ የሥሉስ ቅዱስ እግዚአብሔር ሀሳብ ነበር። ቅዱስ ጴጥሮስ

“ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ” (1ቆሮ. 1፥18-21)

አባት ለልጆቹ ብዙ መልካም ሀሳብና ዕቅድ ቢያስብም ልጆች ግን የአባታቸውን ልብ ካለመረዳትና ካለማስተዋል የተነሣ በራሳቸው መንገድ ሄደው ሊጠፉ ይችላሉ። የጠፋው ልጅ ታሪክ ለዚሁ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው (ሉቃስ 15)። “ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም፤ እናንተም ትጠሩኛለችሁ፥ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፥ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። ከእናንተም ዘንድ እገኛለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ምርኮአችሁንም እመልሳለሁ፥ ከአሕዛብም ሁሉ ዘንድ እናንተንም ካሳደድሁበት ስፍራ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ” (ኤር. 29፥11-14) ነው የሚለው። በአዲስ ኪዳንም ያዕቆብ “ለፍጥረቱ የበኵራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን” (ያዕ. 1፥18)። እግዚአብሔር ስለ እኔ ያስባል ማለት በራሱ ልብን ያሳርፋል፣ ከመቅበዝበዝና ከጭንቀትም ያድናል። አዎን እግዚአብሔር ስለ አንተ፣ አንቺ፣ እኛ ያስባል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *