የጥሞና ቃል ክፍል 18

“እነሆ፥ እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ምስጉን ነው። ስለዚህ ሁሉን የሚችለውን የአምላክን ተግሣጽ አትናቅ።
እርሱ ይሰብራል፥ ይጠግንማል ያቈስላል፥ እጆቹም ይፈውሳሉ” ኢዮብ 5፥17-18

               ይህ ቃል በኢዮብ መጽሐፍ ከሚገኙ አስደናቂ እውነቶች አንዱ ነው። እርስዎ አሁን ያሉበት ሁኔታ ሰው ላያውቅ ይችላል። ከደረሰብዎትም ነገር የተነሣ “ለምን?” የሚል ብቻ ሳይሆን “መጨረሻውስ ምን ይሆን?” የሚል ሥጋት ያለበት ጥያቄ በልብዎ ሊመላለስ ይችላል። ምናልባት የእግዚአብሔር ተግሣጽ ይሆን ወይ? ይህ ከሆነ በእርግጥ ማመስገን ይገባል፣ ምክንያቱ እግዚአብሔር የሚወደውን ይገሥጻልና። በአዲስ ኪዳን የዕብራውያን ጸሐፊም እንዲህ ይላል፦ “እንደ ልጆችም ከእናንተ ጋር። ልጄ ሆይ፥ የጌታን ቅጣት አታቅልል፥ በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም፤ ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና፥ የሚቀበለውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል ብሎ የሚነጋገረውን ምክር ረስታችኋል” ይላል።
ለመሆኑ እግዚአብሔር ለምን ይሠብራል? በእርግጥ የእግዚአብሔር ጥበብና መለኮታዊ አሠራሩ እጅግ ጥልቅ ስለሆነ እርሱ ብቻ ያውቀዋል። አማኞች ግን ማስተዋል ያለባቸው “ነገር ሁሉ ለበጎ” እንደሚያደርገው፣ እንዲያውም በኤርምያስ መጽሐፍ ምዕራፍ 18 ላይ እንደተጻፈው አንድ ሸክላ ከጭቃ የሠራው ዕቃ ቢበላሽበት “እንደ ወደደ መልሶ ሌላ ዕቃ አድርጎ ሠራው” ይላል። ደህና ዕቃ አድርጎ አሳምሮ እንደገና ሊሠራን ይሆናል የሚሰብረን። ሰብሮም አይተውም ይጠግናል፣ አቍስሎም አይተውም “እጆቹ ይፈውሳሉ”። ሆሴዕም “ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ እርሱ ሰብሮናል፣ እርሱም ይፈውሰናል እርሱ መትቶናል፥ እርሱም ይጠግነናል” (ሆሴዕ 6፥1)። ስለሆነም እግዚአብ|ሔርን በትዕግስትና በእምነት ይጠብቁት፤ የመሰበር ጊዜ አልፎ የመጠገን ጊዜ አለ፣ የመቍሰል ግዜም አልፎ የመፈወስ ጊዜ አለ። የእግዚአብሔር ቃል “እነሆ ክረምት አለፈ፣ የዜማም ጊዚ ደረሰ” ይላልና – የቁዘማና የትካዜ ጊዜ አልፎ የዝማሬ ጊዜ በፊትዎ አለ! “አቤቱ፥ አንተ መብራቴ ነህና እግዚአብሔርም ጨለማዬን ያበራል” (2ሳሙ. 22፥29)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *