የጥሞና ቃል ክፍል 19

“እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት፥ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፥

በእርሱ እናቅርብለት” ዕብ. 13፥15

ገና ልጅ እያለሁ ክረምት ት/ቤት ተዘግቶ ከነበርኩበት ከተማ ሌላ ትንሽ ከተማ ወደሚኖሩ ዘመዶች ሄጄ የገጠመኝ እስካሁን አልረሳውም። መንደሩ የተጠባበቁ ቤቶች ያሉበት ነበር። ካረፍሁበት ቤት ወዲያ ሌሊት ሌሊት በግምት በየግማሽ ሰዓት ከማቃሰት ጋር የተቀላቀለ “ተመስገን . . .ተመስገን” የሚል የአዛውንት ድምጽ ይሰማል። “ተመስገን” ሲሉ በጣም እየጮሁ ስለነበር ለጊዜው እንቅልፍ ነሳኝ። እኔም ምናለበት እኚሁ ሰው ዝም ቢሉና ብተኛበት የሚል የማጕረምረም ስሜት ተሰማኝ። እዚያ ቦታ የቆየሁት ለአንድ ወር ነበር፣ ይህም ድምጽ በየሌሊቱ ዘወትር እሰማው ነበርና በኋላ ለመድኩት። አንድ ቀን እኚሁ ሰው ወዳሉብት ቤት ከዘመድ ጋር የመሄድ እድል አጋጠመኝና በአካል ላገኛቸው ቻልኩኝ። በጨዋታ መሃል “አባባ ሌሊት ሌሊት “ተመስገን” እያሉ ባለማቋረጥ የሚጮሁት ለምንድነው?” ብዬ ጠየቅኋቸው። እርሳቸውም “ልጄ ሆይ እድሜዬ ከዘጠና በላይ ነው፤ ከቤት ብዙም አልወጣም፤ ብዙ ጤናም አይሰማኝም፤ በአንድ ጎኔ ተኝቼ ትንሽ ሽልብ አድርጎኝ ስነሳ በሌላው ጎኔ ተገልብጬ ለመተኛት መንቃቴ ለኔ ትልቅ እድል ነው፤ በዚያው እንደተኛሁ እኮ መሞትም ሊኖር ይችላል፣ ላልነቃም፣ ይህችንም ዓለም ተመልሼ ልላያት እችላለሁ። ነገር ግን አምላኬ ያችን ሰዓት በእድሜየ ላይ ጨምሮልኝ፣ ተኝቼ ለመንቃትና በሌላወ ጎኔ ለመገላበጥ ዕድል ስለሰጠኝ ላመሰግነው ይገባኛል”። ያኔ ጌታን ባላውቅም የአዛውንቱ ጨዋታ ግን በልቤ ውስጥ ቀርቶ ዛሬ ሳስበው በጣም ያስደንቀኛል።

ጀንበር ወጥታ እስክትጠልቅ ድረስ ቀኑን ሙሉ በመራገም የሚውሉ ሰዎች ጥቂት አይደሉም። በተለይ በዚህ በምዕራቡ ዓለም በእንግሊዝኛ ፊደል “ኤፍ” የሚጀምር አስጸያፊ ቃል በንግግራቸው እየቀላቀሉ መናገር የብዙዎች ልማድ ሆኖ ይሰማል። ምናልባት ዳዊት “በአፋቸው እውነት የለምና፥ ልባቸውም ከንቱ ነው ጕሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው

(መዝ. 5፥9) የሚለው ስለ እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ይሆን?

እኛ ግን ለማመስገን ተጠርተናል። የምናመሰግነበትም ብዙ ምክንያት አለን። ትናንትን አሳልፎ ለዛሬ ያበቃን ጌታ፣ ማለዳ ማለዳ አዲስ በሆነው ምሕረቱና በብዙ ታማንነቱ የጠበቀን ጌታ ሊመሰገን ይገባዋል። በሰላም ገብተን መውጣታችን፣ ተኝተን መነሳታችን ምክንያት ጌታን ልናመሰግን ይገባል። ምስጋና ሁሉ ሲመቻች ጊዜም ብቻ አይደለም፣ ባልተመቸም ጊዜ ጭምር እንጂ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ምሳሌዎችን እናያለን። ኢዮብ ያለውን ሁሉ ካጣ በኋላ በተለይ የአሥር ልጆቹን ሞት ከተረዳ በኋላም ቢሆን ከማመሥገን አልተቆጠበም። “ራቁቴን ከእናቴ ማኅፀን ወጥቻለሁ፥ ራቁቴንም ወደዚያ እመለሳለሁ እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሣ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን” (ኢዮብ 1፥21) ቅዱስ ዳዊት “እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እባርከዋለሁ፥ ምስጋናውንም ዘወትር በአፌ ነው” (መዝ. 34፥1)። “ሁልጊዜ” የሚለውን ቃል ልብ ይበሉ። ይህ ቀን ለእርስዎም የምስጋና ዕለት ይሁንልዎት! ደግሞም በምስጋና ውስጥ ተአምራት አለ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *